የክልሉ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የደብረ ብርሃን ‘መሶብ’ አገልግሎትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በምረቃ ስነ-ሰርዓቱ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፣ ደብረ ብርሃን ብርሃን የወደቀባት የብርሃን ከተማ መሆኗን ገልጸው፤ ንጉሠ ነገሥት ዘርአ ያዕቆብ የመሰረቱት ይህቺ አንጋፋ ከተማ የእውቀት፣ የጥበብ፣ የህግና ስርዓት ከተማ እንደነበረች ተናግረዋል።
የንጉሠ ነገሥት ዘርአ ያዕቆብ ከተማ የሆነችው ደብረ ብርሃን ያለፈውን ታሪኳን ጠብቃ ከዘመናዊነት ጋር እንደምትገናኝ እና ለትውልድ የሚበቁ ስራዎችን እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማው የተመረቁ በርካታ የልማት ስራዎች ከተማዋን ውብ፣ ንጹህና ለኑሮ ምቹ እንደሚያደርጓቸው ተናግረዋል። ደብረ ብርሃን ከተማ በኮሪደር ልማት ታሪክ እየተገነባች መሆኗን የገለጹ ሲሆን፣ የኮሪደር ልማት ስራውም በ2019 በጀት ዓመት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
‘መሶብ’ የተሰኘው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን እና ለስላሳ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል። መሶብ አብሮ የመብላትና የመሰብሰብ ምልክት መሆኑን የገለጹት የመጀመሪያው ምክትል ከንቲባ፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎቱም ተቋማት በአንድ ላይ ሆነው ማገልገል እንዲችሉ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
‘መሶብ’ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በከተማው ውስጥ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንደሚችል ተጠቁሟል። ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም እንደሚገነቡ አመልክተዋል። በከተማዋ የተገነባው የፍሳሽ ማስወገጃ ፕሮጀክት ንጹህ ከተማ እውን እንዲሆን እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የከተማዋን ልማት ያገናዘቡ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመጀመሪያው ምክትል ከንቲባ ጠቁመዋል። ፕሮጀክቶቹ የተገነቡት በመንግስትና በህዝብ ትብብር ነው።
አሚኮ (Amico) እንደዘገበው፤ የከተማዋን እድገትና ዘመናዊነት እውን የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን ላከናወኑ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።