News Details

በደብረ ብርሃን ከተማ በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ተጀመረ፤

Featured Image


​ደብረ ብርሃን፤ ጥቅምት 23/2019 ዓ.ም (ደብመኮ)፦በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ በማቀናጀት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ የስልጠና መድረክ መጀመሩ ተገለጸ። 

ስልጠናውን ያዘጋጀው የከተማው ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ሲሆን፣ በማዕከሉ አገልግሎት ለሚሰጡ የተቋማት ባለሙያዎች  ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

​የመምሪያው ኃላፊ አቶ እስክንድር ገብረሚካኤል በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፣ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ሃብት በመመደብ የመሶብ አንድ ማዕከል ህንፃን የገነባው ደረጃውን የጠበቀና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋዮችን ቅሬታ በዘላቂነት ለመፍታት ነው ብለዋል።

አዲሱ ማዕከል ዘመናዊ ቴክኖሎጂና አስፈላጊ ግብዓቶች የተሟሉለት በመሆኑ፣ ባለሙያዎች የተመቻቸላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የህብረተሰቡን እርካታ የሚያረጋግጥ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 ህንፃ መገንባቱና ግብዓት ማሟላቱ በራሱ በቂ ባለመሆኑ ባለሙያዎችን በክህሎት ማበቃት አስፈላጊ በመሆኑ ስልጠናው መዘጋጀቱንም አብራርተዋል።

​በሌላ በኩል የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታደለ ልይለት በበኩላቸው፣ የተቋማትን አገልግሎት በአንድ ማዕከል በማደራጀት የህብረተሰቡን እንግልት ለማስቀረትና መልካም አስተዳደርን ለማሰፈን ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

​በክልሉ እስካሁን በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በወልዲያ፣ በደብረ ታቦር እና በጎንደር ከተሞች የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ያስታወሱት ኃላፊው፤ የደብረ ብርሃን ማዕከል 7ኛው ሆኖ ስራ መጀመሩ ለተገልጋዩ ሕዝብ ትልቅ የምስራች መሆኑን ጠቁመዋል። አክለውም ማዕከሉ የታለመለትን  ግብ እንዲመታ ሰልጣኝ ባለሙያዎች ስልጠናውን በትኩረት በመከታተል የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ  ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የሪፎርም ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳላማው ይታይህ በመሶብ ምንነት፣አገልግሎት አሰጣጥ፣የሙያተኞች ስነ ምግባርና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።